መግቢያ
ይህ የቁርአንና የፍቺውን ትርጉም በአማርኛ የተዘጋጀው የተለያዩ የተፍሲር ኪታቦችን ዋቢ በማድረግ ነው። የተጠቀምኩት የትርጉም ስልት ቀጥተኛ የቁርአኑን ትርጉም ከቅንፍ ውጪ በማድረግ፤ የቁርአኑን ፍቺ ትርጉም በነጠላ ቅንፍ ውስጥ በማስገባት ሲሆን በተጨማሪ ማብራሪያዎችን በድርብ ቅንፍ ውስጥ አስገብቻለሁ።
የተለያዩ የቁርአን ኢእራብ ኪታቦችን በመጠቀም ከአማርኛ ሰዋሰው ጋር በማጣጣም የሁለቱንም የቋንቋ ስርአት በተናጥል በመገንዘብና በማዋሃድ እያንዳንዱ የቁርአን መልክት አንባቢ በቀላሉ እንዲረዳ ተደርጓል።
ቁርአን ከአለማቱ ጌታ አላህ በጅብሪል መልክተኛነት ለነብዩ መሐመድ (ሰ.ዓ.ወ.) ከወረደላቸው ዘመን ጀምሮ፤ ለ1400 አመት ቁርአኑን ለመረዳት የአረብኛ ቋንቋ ሊቃውንቶችና ሙፈሲሮች የደከሙባቸውን አስር አይነት የተፍሲር፤ ሶሥት አይነት የኢእራብ (ማለትም የአረብኛ ቋንቋ ሰዋሰው) እና የአረብኛ፤ የአማርኛ፤ የእንግሊዘኛ፤ መዝገበ ቃላቶችን ለትርጉሙ ሥራ ተጠቅሚያለሁ ።
በመጀመርያ ለዚህ ሥራ ለገፋፋኝና ለረዳኝ አላህ ምስጋና ይገባው። በመቀጠል የዲንና የአረብኛ ቋንቋ እውቀት የለገሱኝ ኡስታዞቼ ሁሉ አላህ ለመልካም ሥራቸው ምንዳውን በጀነት ይክፈላቸው በማለት ዱዓ አድርጊያለሁ። በዚህ የቁርአን ሥራ የሚንፀባረቅ ስኬት ካለ ከአላህ ነውና በስኬቱ እኔም ሆንኩኝ ሕዝበ ሙስሊሙ ተጠቃሚ እንዲሆን ጌታዬን አላህ በዱዓዬ እማፀነዋለሁ።
ሰይፈዲን ሐበሻ ያሲን ሻፊ
1437 አመተ ሂጅራ 2016 ዓመተ ልደት
Негізгі бет ETHIODURUS quran amharic tr. AL MAEDA 55 - 120
Пікірлер: 102