✝✞✝ ቂርቆስ ወኢየሉጣ ✝✞✝
††† ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ካሏት ዐበይት ሰማዕታት አንዱ ቅዱስ ቂርቆስ ነው:: በተለይ በዘመነ ሰማዕታት ተነስተው እንደ ከዋክብት ካበሩትም አንዱ ነው:: ቅዱስ ወንጌል እንዲህ ይላል:- "መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ያፈራል::" (ማቴ. 7:17)
መልካም ዛፍ ቅድስት ኢየሉጣ መልካም ፍሬ ብጹዕ ቂርቆስን አፍርታ ተገኝታለችና ክብር ይገባታል:: ቡርክተ ማሕጸንም እንላታለን:: የተባረከ ማሕጸኗ የተባረከ ልጅን ለ9 ወር ተሸክሟልና::
በዚያ ክርስቲያን መሆን መከራ በነበረበት ዘመን ይህንን ደግ ሕጻን እርሷን መስሎ: እርሷንም አህሎ እንዲገኝ አስችላለችና:: አበው በትውፊት እንዳቆዩልን ከሆነ በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን እናታችን ቅድስት ኢየሉጣ ብጹዕ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስን ወልዳለች::
በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን በሮም ግዛት ክርስትና ቢስፋፋም በዚያው ልክ መምለክያነ ጣዖቱ የገነኑ ነበሩ:: በተለይ ከነገሥታቱ ጀምሮ ዋና ዋና የሥልጣን ቦታዎች በአሕዛብ እጅ በመሆናቸው ለዘመኑ ክርስቲያኖች ፈታኝ ነበር::
ማንኛውም ክርስቲያን መሠረታዊ ፍላጐቶቹ እንዲሟሉለት አሕዛብ ላቆሟቸው ጣዖቶች መንበርከክ ነበረበት:: መብቱን ከመገፈፉ ባሻገር "ተበድያለሁ" ብሎ ወደ ፍርድ ቤት ሔዶ እንኩዋ የመጮህ እድል አልነበረውም:: ምክንያቱም የሚሰማው አልነበረም::
በዚያ ላይ በየጊዜው ለክርስቲያኖች ፈታኝ የሆኑ አዋጆች ይወጣሉ:: የክርስትናን ጐዳና ይበልጥ የሚያጠቡ ሕጐችም ዕለት ዕለት ይፈበረኩ ነበር:: ስለዚህም በወቅቱ የነበረ አንድ ክርስቲያን ሃይማኖቱን ከወደደ ወይ እስከ ሞት መታገስ: ካልሆነ ደግሞ ሃገርን ጥሎ በዱር: በገደል መሰደድ ነበረበት::
እውነት ለመናገር ዜና ሰማዕታትን የማያውቅ ክርስቲያን ክርስቶሳዊ ነው ሊባል አይችልም:: ምክንያቱም ዛሬ እንዲህ እንደ ዋዛ የያዝናት ሃይማኖታችን እንዴት እንደ መጣችና ምን እንደ ተከፈለባት አብዛኛው ትውልድ አያውቅምና::
ሕጻኑ ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ብጽዕት ኢየሉጣም የዚህ ዘመን (የዘመነ ሰማዕታት) ፍሬ ናቸው:: በጊዜው በሮም ግዛት ሥር እስክንድሮስ የሚሉት ክፉ ንጉሥ ነግሦ ነበርና ብዙ ክርስቲያኖች ተሰደዱ:: ጣዖትን ላለማምለክም ተሰው::
በዚህ ጊዜ አንጌቤናይት (ኢጣልያዊት) ብጽዕት ኢየሉጣም በመበለትነት (ባሏ በሕይወት ባለ መኖሩ) ትኖር ነበር:: ልጇ ቅዱስ ቂርቆስ ምንም ገና 3 ዓመቱ ቢሆንም ነገረ ሃይማኖትን ታስተምረው: ፍቅረ ክርስቶስን ትስልበት ነበር::
እስክንድሮስ የክህደት አዋጅን ሲያውጅም ቅድስቲቱ ለሕጻን ልጇ ራርታ ሽሽትን መረጠች:: ሃብት ንብረቷን: ወገንና ርስቷንም ትታ: ሕጻን ልጇን ተሸክማ ተሰደደች:: መከራው ግን በሔደችበት አለቀቃትም::
እስክንድሮስ ተከትሎ ባለችበት ቦታም አገኛት:: ወታደሮች ልጇን ሳያገኙ እርሷን ብቻ ይዘው ወደ መኮንኑ አቀረቧት:: መኮንኑም "ስምሽን ንገሪኝ" ቢላት "ስሜ ክርስቲያን ነው" አለችው:: ተቆጥቶ "ትክክለኛውን ስምሽን ተናገሪ" ቢላት "እውነተኛው ስሜ ክርስቲያን ነው:: ሞክሼ (ሞክሲ) ስም ከፈለግህ ኢየሉጣ እባላለሁ" አለችው::
"ለጣዖት ልትሰግጂ ይገባል" ሲላትም "እውነትን ይነግረን ዘንድ የ3 ዓመት ሕጻን ፈልገህ አምጣና ተረዳ" ስላለችው ወታደሮቹን እንዲፈልጉ ላካቸው:: የሃገሩ ሰዎች ልጆቻቸውን ስለደበቁ የተገኘ ቅዱስ ቂርቆስ ነበር::
ቅዱሱ ሕጻን በወታደሮች ተይዞ ሲቀርብ መልኩ ያበራ ነበርና መኮንኑ "በሐከ ፍሡሕ ሕጻን - ደስ የተሰኘህ ሕጻን እንዴት ነህ" ቢለው "ትክክል ነህ! እኔ በጌታየ ክርስቶስ ዘንድ ደስታ ይጠብቀኛል:: አንተ ግን በክህደትህ ወደ ገሃነም ትወርዳለህ" አለው::
በሕጻኑ ድፍረት የደነገጠው መኮንኑ በብስጭት "እሺ! ስምህን ንገረኝ" አለው:: ያን ጊዜ "ከንጹሕ ምንጭ የተቀዳ: ስሜ ክርስቲያን ነው:: እናቴ የሰየመችኝን ከፈለክ ግን ቂርቆስ ነው" ሲል መለሰለት::
ከዚያም እየደጋገመ "እኔ ክርስቲያን ነኝ" ብሎ በመጮሁ መኮንኑ ስቃይን በቅዱሱ ሕጻን እና በቡርክት እናቱ ላይ አዘዘ:: ከዚህ በሁዋላ በእነርሱ ላይ የተፈጸመውን ግፍና የወረደባቸውን የመከራ ዶፍ እናገር (እጽፍ) ዘንድ ግን የሚቻለኝ አይመስለኝም::
በግርፋት የጀመረ ስቃይ ሊሰሙት ወደ ሚጨንቅ መከራ ቀጠለ::
*7 ብረት አግለው በዐይናቸው: በጆሯቸው: በአፋቸውና በልባቸው ከተቱ::
*በ4 ችንካሮች ላይ አስቀመጧቸው::
*በእሳት አቃጠሏቸው::
*ጸጉራቸውን ከቆዳቸው ጋር ገፈፉ::
*ከዚህ በላይ ብዙ ስቃይንም አመጡባቸው::
እናትና ልጅ ግን ለክርስቶስ ታምነዋልና ጸኑ:: ቅድስት ኢየሉጣ ብትደነግጥ ልጇ አጸናት:: ከብዙ ስቃይና መከራ በሁዋላም በዚህች ዕለት በሰማዕትነት ሲያርፉ ጌታ እንደ ቃሉ የሕጻኑን ሥጋ በሠረገላ ኤልያስ አኑሮታል:: ለእኛ የሚጠቅም ብዙ ቃል ኪዳንንም ሰጥቶታል::
Негізгі бет Ойын-сауық ሕጻኑ ቅዱስ ቂርቆስ እና ቅድስት ኢየሉጣ
Пікірлер: 178